«

»

Okt 12

Beitrag drucken

የእረኛውን ድምፅ ለዩ !!

geበጎች የእረኛቸውን ድምጽ ሲለዩ ኑ ሲባሉ ድምጽን እየሰሙ ይከተላሉ ። እረኛው በድምጹ ሊጣራ ይችላል አልሰማ ያሉትን ደግም ወይ በዱላ ካልሆነም ዘግቶ በመተው ከባሰም ምግብን በመከልከል በመቅጣት ሊያናግራቸው ይሞክራል ።
ከበጎቹ መሀል ደግ የሆነው በግ በጥሪው ብቻ ሰምቶ ወደ ተፈለገው ቦታ ይሰማራል እረኛውም አስፈላጊ ከሆነው እና የተመቻቸው ቦታ ላይ ያሰማራዋል ከመልካሙ ምግብ ያጠግበዋል ከንጹሁም ውሃ ያረካዋል ። መልካሙን ሁሉ ያሳየዋል ። እርሱ እንደሚፈልገው ሆኖ አግኝቶታልና ይወደዋል አምኗልና ሁሉ ይከናወንለታል ከክፉም ጠላት ይጠብቀዋል ልክ እንደ ዓይኑ ብሌን ይንከባከበዋል ።
በጎቹን እጅግ ይወዳቸዋልና መልካምም ይሆኑ ዘንድ ሁሌም ይጨነቃል እስኪመለሱም በጥሪው ይቀጥላል ይጣራል ይጣራል። ነገር ግን አልሰማው ብለው ከሕይወታቸው ሊጠፉ ገደል ሊገቡ ከተነሱ ግን ዝም ዓይልም አስር ነጻ ፈቃድ አስር ነጻነት ቢሰጥ እረኛው በጎቹን ለጨለማ አሳልፎ ሊሰጥ አይወድም። ስለዚህም በጎቹን ወንጭፉን አንስቶ እያጮኸ ሊመልሳቸው ይሞክራል ድምጹም ገብቷቸው ቢመለሱ ሁሉን እረስቶ ሊቀበላቸው እጁን ይዘረጋል ። በዚህም ካልተመለሱ በያዘው ዱላ መታ መታ ያረጋቸዋል እንዲጎዱ አይወድምና ለሚሰደው በትር ጥንቃቄን ያደርጋል ። በበትር ባይመለሱም በርሐብ ይቀጣቸዋል በምንም ምክንያት በጎቹ ከእርሱ መንገድ እንዳይቀሩ እረኛው ሁሉን ያደርጋል ። እንቢ ብሎ የጠፋው ግን ገደል ይገባል የጅብም እራት ይሆናል ።
እረኛችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እኛ ከመንገዱ እንዳንስት በተለያየ መንገድ ይናገረናል እኛም ድምጹን ለመስማት ለመለየትም የተዘጋጀን ልንሆን ይገባል። በፍቅሩ መርጦ በራችንን ያንኳኳል ድምጹንም ብንሰማ ደጃችንንም ብንከፍትለት አብሮን እራትን ሊበላ የተዘጋጀ ነው።(ራዕ 3፤20 -21 ) እርሱ በተለያየ መንገድ ይጣራል ።
እረኛው በፍቅር ይጣራል !!

እረኛችን ክርስቶስ በፍቅር ወደ ንስሐ እንመለስ ዘንድ በተለያየ መንገድ ይነግረናል አንድም በመምሕሮች ላይ አድሮ በወንድም እሕቶቻችን እንዲሁም በጓደኞቻችን ውስጥ ሆኖ አልያም ደግሞ ምንም ሳይገባን በበረከቱ ሁሉ ሞልቶ እጅግ በፍቅር በደስታ ሞልቶ ይጠራናል። ( ‹‹መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ።›› ማቴ 3፥1 እንዲል)። በፍቅር ተጠርተው ወደመንገዱ ወደበረቱ የገቡ ምንኛ እድለኞች ናቸው በረከት ሁሉ ከእነርሱ ጋር ነውና ።

እረኛው በወንጭፉ ድምጽ ይጣራል


እረኛው ወንጭፉን ያጮሐል የወንጭፉ መጮህ በጉን ያስደነግጣል እንጂ በቀጥታ ምንም አያደርገውም ። ክርስቶስም እኛ እንማር ዘንድ የዓለምን ጥፋት ያሳየናል ። መገናኛ ብዙሃን ማሕበራዊ ሚድያወች ሁሉ ሁሌም የዓለምን ጥፋት እንጂ ሰላም ሲያወሩ ሰምተን አናቅም ። ዓለም ወደ መጥፋት ከሚገባው በላይ እየተንደረደረች ነው እረኛችንም ይህንን ወንጭፍ አጩሆ እኛ እንድንሰማው እየተጣራ ነው ። ማንም የወንጭፉን ድምጽ ሰምቶ እሚመለስ ቢኖር እረኛው ሊቀበለው በፈገግታ ታጅቦ ይቀበለዋል ። ( ‹‹ከእንቅልፍ እምትነሱበት ሰዓት አሁን እደደረሰ ዘመኑን እወቁ።›› ሮሜ 13፥11)

እረኛችን በዱላው መታ መታ አያረገ ይጣራል

የሰው ልጅ በፍቅር በማስተማርና ማስደንገጥም አልሰማ ሲል እረኛው አሁንም ለዓለም ለጨለማ ልጆቹን አሳፎ አይሰጥም ይልቁንስ ቆንጠጥ አርጎ ሊያስተምረን ለፈተና አሳልፎ ይሰጠናል ። በሕይወታችን ደስታን ልናጣ እንችላለን ሠላምም ሊጠፋ ይችላል በበሽታ ተይዘን ወደ አልጋ ልንወረወር እንችላለን ። ሁሉም ግን ለበጎ ነው ወደ በረታችን እንመለስ ዘንድ ። እረኛችን በዚህ መልኩም ይጣራል በዚህም ሁሉ እንመለስ ዘንድ እርሱ በተስፋ ከሙሉ ፍቅሩ ጋር ይጠብቀናል ።( ‹‹እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እቀጣቸዋሁ እገስፃቸውማለሁ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ ።›› ራዕ 3፥19)
የአምላክን ጥሪውን ማወቅ መለየት ግን የእኛ ኃላፊነት ነው ። እረኛሕ ሲነግርህ ስማ በሕይወትሕም ደስተኛ ትሆናለህ ። ዛሬ መከራ ውስጥ ትሆናለሕ ሰላምም ፍቅርንም ተነፍገሕ ይሆናል ። ሀፍት ሁሉ ሞልቶሕ ደስታን አጠህ ይሆናል ። በእውቀት ሁሉ መጥቀህ ነገር ግን የአእምሮ ሰላምን አጠሕ ይሆናል በስራ በትዳር ማጣት ጭንቅላትሕ ተወጥሮ ይሆናል ይህ ሁሉ ግን እረኛህ ወደ እርሱ ሊስብሕ እየጠራሕ ይሆናልና ጆሮሕን ክፈት ወደ እርሱም ተመለስ ንስሐም ግባ ያኔ ሰላም ፍቅር ደስታ ወደ አንተ ይመጣሉ ሁሉም ከእርሱ ዘንድ ናቸውና ። ( ሠላሜን እሰጣችኋለሁ ሠላን እተውላችኋለው እኔ እመሰጣችሁ ሠላም ግን ዓለም እደሚሰጣሁ አይደለም ።) ከሞት አላዛርን ያስነሳ አምላክ ምን ይሳነዋ ብለሕ ትረበሻለህ ። ከእርሱ ጋር ስትሆን ሁሉም ያንተ ነው ።
ነገር ግን አንሰማም አልመለስም ብንል ግን እንደ ስጋም ፈቃድ ብንኖር ባትንነቃ ንስሀም ባንገባ እንደ ሌባ ይመጣብናል በማናቸውም ሰዓት እንደሚመጣ አይታወቅምና ያኔ ከንቱ መጮሕ ይሆናል ለሞትም ተላልፈን እንሰጣለን ። ሞትን ብቻ ሳይሆን የሞት ሞትንም እንሞታለን። (ራዕ 3፥3፤ ሮሜ 8፥13 ፤ ሮሜ 6፥23)

 እግዚአብሔር አምላክ እርሱን እምንሰማበት ድምጹንም የምንለይበት ልቦናን ያድለን ።

 

Permanentlink zu diesem Beitrag: http://kidistmariammunich.de/wp1/?p=622