«

»

Apr 27

Beitrag drucken

ሰሙነ ሕማማት !!

  ህማማትቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ በፊት ያለውን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት /የሕማማት ሳምንት/ በማለት ትዘክረዋለች፡፡ ሕማማት የሚለው ቃል “ሐመ፤ ታመመ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን የጌታችንና የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማምና ሞቱ የሚዘከርበት ሳምንት ነው፡፡
በሌላም በኩል ይህ ሳምንት ከአዳም እስከ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ የነበሩ ነፍሳት በሲኦል የቆዩበት የአምስት ሺህ አምስት መቶ የመከራ፣ የፍዳና የኩነኔ ዘመን መታሰቢያ ስለሆነ የሕማማት ሳምንት የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡ እንደዚሁም ይህ ሳምንት “ቅዱስ ሳምንት” ይባላል” ከሌሎች ሳምንቶች ሁሉ የተለየ የከበረ ነውና፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሳምንት በእያንዳንዱ ዕለት ስለ ፍጹም ፍቅር የተከፈለ የመሥዋዕትነት ሥራ ስለ ተሠራበት፣ የሰው ልጆች ደኅንነት ስለ ተፈጸመበት፣ መድኀኔዓለም ስለ እኛ ቤዛ ሆኖ ለመስቀል ሞት ታዛዥ ሆኖ ነፍሱን ስለ ካሠልን “ቅዱስ ሳምንት” ተብሏል፡፡ በተጨማሪም “የመጨረሻ ሳምንት” ተብሎ ይጠራል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሙዓለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመሆኑ ነው፡፡

በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ፤ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡

ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፣ ስብሐተ ነግህ አይደረስም፣ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፣ ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም፡፡ እንዲሁም ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሳዕና ይከናወናሉ፡፡

በግብረ ሕማማት ውስጥ የሚገኙ ባዕድ ቃላት

በግብረ ሕማማት ውስጥ ወደ ግእዝም ሆነ በኋላ ወደ አማርኛ ሳይተረጎሙ የተቀመጡ የዕብራይስጥ፣ የቅብጥ እና የግሪክ ቃላት ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ቃላት ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡

ኪርያላይሶን

ቃሉ የግሪክ ሲሆን አጠራሩ «ኪርዬ ኤሌይሶን» ነው፡፡ «ኪርያ» ማለት «እግዝእትነ» ማለት ሲሆን «ኪርዬ» ማለት ደግሞ «እግዚኦ» ማለት ነው፡፡ ሲጠራም «ኪርዬ ኤሌይሶን» መባል አለበት፡፡ ትርጉሙም «አቤቱ ማረን» ማለት ነው፡፡ «ኪርያላይሶን» የምንለው በተለምዶ ነው፡፡ ይኼውም ኪርዬ ከሚለው «ዬ» ኤላይሶን ከሚለው ደግሞ «ኤ» በመሳሳባቸው በአማርኛ «ያ»ን ፈጥረው ነው፡፡

ናይናን

የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «መሐረነ፣ ማረን» ማለት ነው፡፡

እብኖዲ

የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «አምላክ» ማለት ነው፡፡ «እብኖዲ ናይናን» ሲልም «አምላክ ሆይ ማረን» ማለቱ ነው

ታኦስ

የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «ጌታ፣ አምላክ» ማለት ነው፡፡ «ታኦስ ናይናን» ማለትም «ጌታ ሆይ ማረን» ማለት ነው፡፡

ማስያስ

የዕብራይስጥ ቃል ሲሆነ ትርጉሙ «መሲሕ» ማለት ነው፡፡ «ማስያስ ናይናን» ሲልም «መሲሕ ሆይ ማረን» ማለት ነው

ትስቡጣ

«ዴስፓታ» ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ደግ ገዥ ማለት ነው

አምነስቲቲ ሙኪርያቱ አንቲ ፋሲልያሱ

የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ- አቤቱ በመንግሥትህ አስበኝ» ማለት ነው፡፡

አምንስቲቲ መዓግያ አንቲ ፋሲልያሱ

የቅብጥ ቃል ሲሆን «ተዘከረነ ኦ ቅዱስ በውስተ መንግሥትከ – ቅዱስ ሆይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው

አምንስቲቲ ሙዳሱጣ አንቲ ፋሲልያሱ

የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚአ ኩሉ በውስተ መንግሥትከ- የሁሉ የበላይ የሆንክ ወይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው፡፡

የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊና ቱፊታዊ ክንዋኔዎች

አለመሳሳም፡- በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምን የትክሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማግሰኞ መከሩ አልሰመረላቸውም፡፡ ምክረቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ስለዚህ አይሁድ እያንሾካሾኩ እንሰቀለው ፤እንግለው ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ በዘመነ ፍዳ ወቅት ሠላምና ፍቅር አለመኖሩን የሚገልፅልን በመሆኑ ያንን ለማስታወስ ስላምታ አንለዋወጥም፡፡

ሕፅበተ እግር፡- ጌታ በፍጹም ትህትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ህይወት ማሕተም የሆነውን ምስጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው ጸሎተ ሐሙስ ሕፅበተ እግር ጌታችን በዚህ እለተ እናንተ ለወንድማችሁ እንዲሁ አድርጎ ለማለት የደቀ መዛሙርቱን አግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡

አክፍሎት፡- በሰሙነ ሕማማት እለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሁድ /የትንሳኤ በዓል/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ከዓርብ እስከ ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ማክፈል የብዙዎች ነው፡፡ አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታቸን ያዕቆብ እና ዩሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡

ጉልባን እና ቄጠማ፡- ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጀና የጸሎት ሐመስ እለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብጽ ተሰደው በሚነጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካው ሊጥ እያጋገሩ ቂጣ መብላት ንፎሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓል ይታሰባል፡፡

ጥብጠባ፡- በሰሙነ ሕማማት እለተ ዓርብ ስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሰሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱን በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጠባው የሚደረግለት ሰው በህማማቱ ወቅት የፈጸማ በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እያለ እንዲል ያደርጋል፡፡

ቄጠማ(ቀጤማ)፡- በቀዳም ስዑር ቀሳውቱን ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ አዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠ እና ትንሳኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመኑም ለቤተ ክርስቲን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስተውስ ነው፡፡ በዚህ እለት ልብስ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲቆናትን ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲቃጭሉ መታየታቸው እለተ ትንሳኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

ወስብሀት ለእግዚአብሔር

 

Permanentlink zu diesem Beitrag: http://kidistmariammunich.de/wp1/?p=592